የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ገደብ የታቀደለትን ዓላማ ያሳካ በመሆኑ፣ ገደቡ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ምክረሃሳብ አቅርቦ መጽደቁን ነው ያስታወቀው፡፡
የብድር ዕድገት ገደብ መነሳትን ተከትሎ ተመጣጣኝ የሆነ ጥብቅ የፖሊሲ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግ መሆኑን የጠቀሰው ኮሚቴው በዚህም የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ከ15 በመቶ ወደ 16 በመቶ እንዲያድግ መደረጉን ጠቅሷል፡፡
የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ የመጠባበቂያ ተቀማጭ እንዲተገብር መወሰኑን ያስታወቀው ባንኩ የዋጋ ግሽበት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመገደብ የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ኮሚሽን ምጣኔ ከ2 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 1 ነጥብ 5 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል ብሏል፡፡
በተጨማሪም የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል፤ የገበያ ላይ መተማመን ለመገንባትና የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማሳለጥ፣ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ለባንኮች እንዲሸጡ የሚጠየቀው 50 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲደረግ ኮሚቴው ምክረ ሃሳብ አቅርቦ መጽደቁን ነው ያስታወቀው፡፡
