EthiopiaNews

ከነገ ነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ እስከ መጪው መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡

በየዓመቱ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ለሁለት ወራት ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ ያስታወሰው ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስቸኳይ የሆኑና ጊዜ የማይሰጡ፣ በዜጎች መብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አቤቱታዎችን መመልከት የሚቀጥሉ መሆናቸውንም ነው የጠቀሰው፡፡‎

‎በወንጀል ጉዳዮች፤ ሕፃናት የያዙ ሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የወጣት ጥፋተኞችን የሚመለከቱ የይግባኝ ጉዳዮች፣ ለወንጀል ምርመራ በሚቀርቡ የጊዜ ቀጠሮዎች፣ የዋስትና ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ ክርክሮችና አቤቱታዎች በዚሁ ወቅት የሚታዩ ይሆናል፡፡

‎በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ደግሞ የቀለብና ተያያዥነት ያላቸው የቤተሰብ ጉዳዮች፣ አስቸኳይ መፍትሔ የሚፈልጉ የንግድና ሌሎች አቤቱታዎች፣ በግራ ቀኝ ወገኖች ስምምነት ወይም በአንድ ወገን የሚቀርብ ከመዝገብ ጋር ይያያዝልኝ አቤቱታዎች የሚስተናገዱ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

‎የሰበር አጣሪ ችሎት በመደበኛ ጊዜ የሚያከናውነውን አጣርቶ ውሳኔ የመስጠት ሥራ እስከ ነሐሴ 30 ቀን ድረስ የዳኝነት አገልግሎት መስጠቱን እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡

የተረኛ ችሎት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጳጉሜ 1 ቀን 2018 እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም በከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ደግሞ ከነሐሴ 1 ቀን 2018 እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ችሎት እንደሚቀጥሉም ነው የተገለጸው፡፡