የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአመት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚደርስ ግብይት በባንኩ የዲጂታል አማራጮች እየተከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡
ባንኩ ይህን የገለጸው በቀጣዩ ጥቅምት ወር ለ3ኛ ጊዜ የሚያከብረውን የሳይበር ደህንነት ወር በማስመልከት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
በመግለጫውም በባንኩ የዲጂታል አማራጮች በአመት እስከ 22 ትሪሊየን ብር የሚደርስ ግብይት ይፈጸማል የተባለ ሲሆን ባንኩ ይህን ግብይት ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
የባንኩ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ሴኩሪቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ስዩም ዳምጠው የሳይበር ጥቃት የሚያደርሱ አካላት እንደባንኩ ባሉ ብዙ ሃብት ባለባቸው ተቋማት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ በመጥቀስ ይሄንን ስጋት ለማስወገድ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ከዲጂታል ግብይት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች አብረው ማደጋቸውን የገለፁ ሲሆን ባንኩ ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ስርዓት ለመገንባት ከሚያደርገው ጥረት ጋር በተያያዘ የሳይበር ደህንንት ወርን በየዓመቱ በማክበር በዘርፉ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
