በአማራ ክልል በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በዚሁ ጊዜም በክልሉ የተሰበሰበው ገቢ በተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች እና የጸጥታ ችግሮች ውስጥ ታልፎ በተከናወነ የገቢ አሰባሰብ እንቅስቃሴ በመሆኑ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት ገቢ በድምሩ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ያቀደው ቢሮው ከመደበኛ ገቢ ከ82 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ከከተማ አገልግሎት ገቢ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ነው የገለጸው፡፡
በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተሰበሰበው ገቢ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም የ54 በመቶ እድገት የተመዘገበበት መሆኑን ከአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
