የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በየቡድኖቹ የተጠናቀሩ ምክረ ሃሳቦችን የማጣጣም ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ ይሄን ያሉት እየተካሄደ የሚገኘውን ምክክር አስመልክተው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ምክትል ኮሚሽነሯ በመግለጫቸውም ከስምንቱ ቡድኖች የተውጣጡ 120 የሚጠጉ ተወካዮች ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ምክረ ሃሳቦችን የማጣጣም ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከየቡድኑ የተወጣጡት 15 ተወካዮች፣ በስምንቱ ቡድኖች መካከል የተዘጋጁ ምክረ ሃሳቦች ድግግሞሽ እንዳይኖርባቸው፣ በአንድ ወጥ መልክ እንዲቀርቡ የማጣጣም ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሯ ተወካዮቹ ስለሌሎች ቡድኖች ምክረ ሃሳቦችም ግንዛቤ በመውሰድ እርስ በርስ የሚመካከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሯ የተጣጣሙት ምክረ ሃሳቦች ለስምንቱም ቡድኖች ተመልሰው እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፣ ቡድኖቹም ዛሬ ከሰዓት በኋላ በተሰራው ስራ ላይ ግብዓት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የተሰበሰበው ግብዓት ነገ ላይ ተጠናቅሮ፣ ረቡዕ ዕለት በአራትሺህ ተሳታፊዎች እንደሚጸድቅ ምክትል ኮሚሽነሯ ገልፀዋል።
