በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን መካከል በተደረገ የእርስ በርስ ድብድብ ተሳትፏል የተባለ አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ።
በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይሄን ያለው ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው ሲደባደቡ እና ጥቃት ሲፈፅሙ የሚያሳይ ቪዲዮን ለማጣራት ክትትል እያደረገ መሆኑን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ነው።
ኤምባሲው እስካሁን በተደረገ የመረጃ ማሰባሰብ ሂደት በዚህ ኢሰብአዊ ተግባር እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦች በኢመደበኛ መንገድ ወደ በሳውዲ አረቢያ የገቡ መሆኑን ገልፆ በበረሃማ ገጠራማ አካባቢዎች በመመሸግ ምክኒያታቸው በግልፅ ባልታወቀ ሁኔታ መጋጨታቸውን አሳውቋል።
በዚህም አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኤምባሲው ገልጿል።
ኤምባሲው ጉዳዩን አጣርቶ ከምንጩ ለማድረቅ እና በዚህ ተግባር የተሳተፉ ሰዎችን ለህግ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው ብሏል።
ኤምባሲው ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ በሪያድ ከሚገኙ የሃገር ሽማግሌዎች ጋር እየሰራ መሆኑን እና ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚያግዝ መረጃ ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል።መረጃው በሳውዲ አረቢያ ሪያድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘ ነው።
