በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር በአዲስ አበባ የተወያዩት ረዳት ሚኒስትሩ በህብረቱና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸው ተገልጿል፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ በውይይቱ ህብረቱ ከአሜሪካ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ያለው መሆኑን አንስተው ይሄንኑ ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ በበኩላቸው አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልፀው የትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪካ ህብረት እና አባል ሃገራት ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በቅርቡ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት ፍራንክ ጋርሺያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና የጋራ የጸጥታ እና ኢኮኖሚ አጋርነቶችን ለማጎልበት እንደሆነ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ባለስልጣኑ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከቀናት በፊት በዛምቢያ ጉብኝት ያደረጉት ረዳት ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የሚኖራቸውን ቆይታ ሲያጠናቅቁ ወደ ኬንያ በመጓዝ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋርም ይመክራሉ ተብሏል፡፡
