የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በባለስልጣኑ ስም ከሚላኩ ሀሰተኛ የኢሜል መልዕክቶች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ አሳሰበ፡፡
ቀደም ሲል በባለሥልጣኑ አዘጋጅነት በተካሄዱ የኦንላይን ኢንቨስተር የትምህርት ፕሮግራሞች ለተመዘገቡ ወይም ለተሳተፉ ግለሰቦች፤ እንዲሁም ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የባለሥልጣኑን ስም በሐሰት በመጠቀም ወይም ያለ ባለሥልጣኑ እውቅና፣ ተሳትፎና ፈቃድ ከባለሥልጣኑ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አስመስለው የሚቀርቡ መልዕክቶች እየተሰራጩ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በባለሥልጣኑ ስም እየተሰራጩ ከሚገኙ ሀሰተኛ መልዕክቶች መካከል በባለሥልጣኑ የኦንላይን የኢንቨስትመንት ትምህርት መድረክ ላይ የተመዘገቡ ወይም የተሳተፉ ግለሰቦች አዲስ የታቀደ የብድር እና ቁጠባ የህብረት ሥራ ማህበር መስራች አባላት እንዲሆኑ የሚጋብዝ መልዕክት ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
ባለሥልጣኑ በዚያ ኢሜይል ውስጥ ከተጠቀሰው አስተባባሪ ወይም መስራቾች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ጠቅሶ የኢንቨስትመንት ትምህርት ተሳታፊዎች አድራሻ በዚህ መልኩ እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደቻለ እያጣራ እንደሚገኝም ተናግሯል፡፡
ህብረተሰቡ ማንኛውም መልዕክት ከባለሥልጣኑ የወጣ መሆኑን ለማረጋገጥ፤ ወይም በዚህ መልዕክት ላይ የተገለጸውን ዓይነት አጠራጣሪ መልዕክቶች ሲደርሱት ራሱን እንዲጠብቅም ነው ያሳሰበው፡፡
