የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በከተማዋ በህገወጥ የመኪና ሽያጭ በተሰማሩ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ተከትሎ መኪናዎቻቸውን የሰወሩ አስመጪዎች ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡
የመኪና አስመጪነት ፍቃድ ሳይኖራቸው በኮሚሽን ስራ ፍቃድ የመኪና መሸጫዎችን በመክፈት ሲሸጡ የነበሩ የኮሚሽን ሰራተኞችን ፍቃድ ማገዱንና የሚሸጡትን መኪና ለአስመጪዎች እንዲመልሱ ማድረጉን የገለጸው ቢሮው አሰራሩን በማይከተሉ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ ተከትሎ በየቦታው ባለ መጋዘን መኪኖች የሸሸጉ ግለሰቦች መኖራቸውን የጠቀሰው ቢሮው በከተማ ደረጃ በተዋቀረው ግብረ ሃይል የመጋዘን ፍተሻ ማድረጉን እንደሚቀጥልም ነው የጠቀሰው፡፡
በዚህ ተግባር የተሰማሩ አስመጪዎች በራሳቸው መንገድ ወደ ህጋዊ አሰራሩ እንዲገቡ ጥሪ ያቀረበው ቢሮው ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሚደረገው ፍተሻ መኪኖቹ ከተያዙ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
