የነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 15.1 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ይህ በነሐሴ 2017 ዓ.ም ከነበረው 13.6 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱን የጠቀሰው አገልግሎቱ ምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች ዋጋ በ14.9 በመቶ መጨመራቸውን ነው አገልግሎቱ የገለጸው፡፡
በዋናነት አትክልት በ12.1 በመቶ፣ ስጋ በ22.6 በመቶ፣ የወተት ተዋፅኦች እና እንቁላል 18.7 በመቶ ፣ፍራፍሬ በ19.1 በመቶ፣ ዘይት በ18 .8 በመቶ እንዲሁም ማር እና ቸኮሌት 38.3 በመቶ የዋጋ ግሽበት በመኖሩ ይህ ጭማሪ መመዝገቡን አገልግሎቱ ገልጿል።
ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት ደግሞ 15.4 በመቶ መድረሱም ነው የተነገረው፡፡
በትራንስፖርት ዘርፍ ደግሞ 15.6 በመቶ፣ በኮሙዩኒኬሸን 8.0 በመቶ፣ በምግብ ቤቶችና ሆቴሎች 15.3 በመቶ እንዲሁም በሌሎች እቃዎችና አገልግሎቶች የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ 19.3 በመቶ ሆኖ መመዝገቡ ተገልጿል።
የሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 15.3 በመቶ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
መረጃው ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የተገኘ ነው።
