እስራኤል በዌስት ባንክ በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰው ጥቃት እና የመሬት ነጠቃ እጅግ አሳፋሪ ነው ስትል ፈረንሳይ ወቀሰች።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት፣በአክራሪ እስራኤላውያን አማካኝነት በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል።
ይህ ውንጀላ የቀረበው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ፣ ሀማስ በማይንቀሳቀስበት ዌስት ባንክ በየቀኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ በማጠናከር፣ የእስራኤል መንግስት አካሄድ ሀማስን እንደማያዳክምና ሀማስን መዋጋት በስፍራው ለሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች መሸፈኛ ሊሆን እንደማይችል ነው የተናገሩት።
በሌላ በኩል ሚኒስትሩ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ በፈረንሳይ እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ላይ የምታደርጋቸው የጥላቻ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውንም አስጠንቅቀዋል።
