ርዕሰ ብሔር ታዬ አጽቀሥላሴ የኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ እያደገ መምጣቱን ተናገሩ።
የሕዝብ እንደራሴዎች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባቸውን ማድረጋቸው ነው የተነገረው።
ርዕሰ ብሔሩ ታዬ አጽቀሥላሴ ለምክር ቤቶቹ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የኢትዮጵያ የልማት እና እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባህር በር ማግኘት የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ የባህር በር ባለቤት ለመሆን ያላት ፍላጎት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያድግ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።
ይህ የኢትዮጵያ መሻት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋራ በጋራ የማደግና የመልማት ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤት የመሆን ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲሳካ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
