EthiopiaNews

የፌደራል መንግስት ስራ አስፈፃሚ አካላት ስያሜ እና አደረጃጀት የሚቀይር ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቅረቡ ተነገረ።

ምክር ቤቱ ይሄን ያለው ዛሬ እያካሄደ ባለው አንደኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ነው።

በረቂቅ አዋጁ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ቁጥር 22 ሆኖ የሚቀጥል ነው ተብሏል።

በሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ የስያሜ ለውጥ እንዲደረግ እና ሁለት ሚኒስቴር መ/ቤቶች ደግሞ እንደ አዲስ እንዲቋቋሙ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለም/ቤቱ ቀርቧል።

እንደ አዲስ የተቋቋሙት ሁለት ሚኒስቴር መ/ቤቶች ቀድሞ “የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር” የነበረው በአዲሱ “የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር” በሚል እና ቀድሞ “የቱሪዝም ሚኒስቴር” የነበረው በአዲሱ “የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር” በሚል መቋቋማቸው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ወደ «ብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር»፤ እንዲሁም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ወደ «ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር» በሚል የስያሜ ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ላይ ማሻሻያ ያስፈለገበት ምክንያት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና ከተሰጣቸው ተልዕኮ ጋር ይበልጥ እንዲጣጣሙ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እያቀረቡ እንደሚገኙ የም/ቤቱ መረጃ ያሳያል።