ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፈው በጀት ዓመት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር መክፈሉንና አምርቶ ለውጭ ገበያ ባቀረበው ምርት ከ390 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱ ተገልጿል።
ተቋሙ በአሁኑ አመትም ምርቶቹንና አገልግሎቶቹን ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስርን ለማጠናከርና ያለውን የማኅበራዊ ኃላፊነት ተሳትፎ ለማሳየት ያዘጋጀው የሚድሮክ ሳምንት አውደ ርዕይ ከጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ቀናት እንደሚካሄድ አስታውቋል።
በአውደ ርዕዩ ሁሉም የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድርጅቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው በመቅረብ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ ተገልጿል።
አውደ ርዕዩ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸውን ሥራዎችና ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ለማሳየት እድል እንደሚፈጥርም ተገልጾ የፓናል ውይይት እንደሚኖርም ተጠቁሟል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ማበርከቱ የተገለጸ ሲሆን ተቋሙ ከ45 በላይ ኩባንያዎችን በውስጡ በማቀፍ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በሆስፒታሊቲ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽንና በሪል እስቴት ዘርፎች እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በሥራ ዕድል ፈጠራም ከ80 ሺህ በላይ ዜጎችን በመቅጠር አስተዋጽኦ ሲያበረክት ተቋሙ ከሚያገኘው ትርፍ 10 በመቶውን ለበጎ አድራጎት በማዋል የማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑም ተጠቁሟል።
