EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በወጣት ዮርዳኖስ አምበሉ ግድያ ወንጀል በተጠረጠረው ኢዮብ እንዳለ ላይ ምርመራ መቀጠሉን አስታወቀ።

ፖሊስ በወጣት ዮርዳኖስ ግድያ የተጠረጠረው ተጠርጣሪ ኢዮብ እንዳለ እንደሚባልና የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ/ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሠባት ልዩ ቦታው ብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት (ወመዘክር ) ቅጥር ግቢ ውስጥ ከምሽቱ 2፡10 ሠዓት አካባቢ መሆኑን ገልጿል።

በግድያ ወንጀል የተከሰሰው ተጠርጣሪው ኢዮብ እንዳለ ለፖሊስ በሰጠው ቃል፣ ከሟች ዮርዳኖስ አምበሉ ጋር ” ከአንድ ዓመት በላይ ትውውቅ አለን ፤ በፍቅር ግንኙነትም ቆይተናል ” ብሏል።

” ከጊዜ ወደ ጊዜ የባህሪዋ መለዋወጥና በስልክ የምናደርገውን የድምፅ ድውውሎሽ ወደ ፅሁፍ መልዕክት በመቀየሯ በሌላ ሰው እንድጠረጥራት አድርጎኛል ” ሲልም ተጠርጣሪው ገልጿል።

” (መስከረም 26) ሌላም ጊዜ ወደምንሄድበት ብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት (ወመዘክር) ለመገናኘት ከቀኑ 10፡00 ሠዓት አካባቢ ቄራ አካባቢ ተቀጣጥረን ነበር ” ብሏል።

” ቄራ አካባቢ በቀጠሮአችን ሰዓት ስላረፈደች የሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ በመግዛት ደብቄ ይዤ ጠበቅኳት ስትመጣም የራይድ ከፍላ ወደ ወመዘክር ሄድን ” ሲል ገልጿል።

” ከዚህ ቀደም ወደምንቀመጥበት ቦታ ሄደን አረፍ ብለን ስናወራ ነበር። በመሀላችን በንግግር ያለ መግባባት በመፈጠሩ እና በሌላ ሰው ጥቃት ልታደርስብኝ ትችላለች በሚል ጥርጣሬ ለወንጀሉ ድርጊት በገዛሁት ቢላዋ አራት ቦታ ወግቻታለሁ ” ሲል ተጠርጣሪው ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል።

እንደ ፖሊስ መረጃ፣ ተከሳሹ ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ስልኩን በማጥፋት ከግቢው በማምለጥ ወደ ሀዋሳ ጉዞ ለማድረግ ሞጆ ላይ ቆይቶ፤ ኋላም ስልኩን በመክፈት ወደ አዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ተመልሷል።

ፖሊስ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክትትል አድርጎ ከተደበቀበት አካባቢ 48 ሠዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

ሟች በወቅቱ አደጋው እንደደረሰባት በግቢው ውስጥ የሚገኙት አራት የጥበቃ ባለሙያዎች በአካባቢው ወደሚገኘው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መውሰድ ሲገባቸው ይህን ኃላፊነት ያልተወጡ በመሆኑና ግለሰቡም ወደ ግቢው ሲገባ ፍተሻ ባለማድረጋቸው ምክንያት ሁሉም ታስረዋል።

በወቅቱ በግቢው ውስጥ የነበሩ ሌሎችም 36 ሰዎችም ታስረው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል።

የተከሳሽ ወላጅ አባት አቶ እንዳለ ልጃቸውን ለማሸሽ ባደረጉት ሙከራ ተይዘው ምርመራ ሲጣራባቸው ቆይቶ በፍ/ቤት ዋስ መለቀቃቸውን ፖሊስ አሳውቋል።

ወንጀል በሚፈፀምበት ወቅት እያዩ አለማስቆም ፣ ወንጀል የተፈፀመበትንና አደጋ የደረሰበትን ግለሰብ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ አለማድረግ ወይም አለመርዳት የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ፖሊስ አሳስቧል።

መረጃው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘ ነው።