EthiopiaNews

የተሻሻለው የጉምሩክ አዋጅ የንግዱን ማህበረሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ለውጦችን ማካተቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ወደ አገር ለሚገቡ ዕቃዎች መከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ በአንድ ጊዜ መክፈል የማይችል ነጋዴ፣ ዕቃዎቹ በክፍልፋይ እንዲለቀቁለት ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን በዚህም መሠረት ለሚለቀቁት ዕቃዎች የሚጠየቀውን ቀረጥና ታክስ በመክፈል ዕቃዎቹን ማስለቀቅ ይቻላል ተብሏል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም አንድ ነጋዴ በርካታ ኮንቴይነሮችን በአንድ ሰነድ ካስመጣ፣ ዕቃዎቹ ለነፃ ዝውውር የሚለቀቁት የሁሉንም ዕቃዎች ቀረጥ ሙሉ በሙሉ ከከፈለ ወይም ተመጣጣኝ ማስያዣ ካስያዘ በኋላ እንደነበር ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በቀድሞው አዋጅ በየብስ ተጓጉዘው አገር ውስጥ ለሚደርሱ ዕቃዎች አስፈላጊውን የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት በማጠናቀቅ ለነፃ ዝውውር እንዲለቀቁ የተደነገገው የ15 ቀናት የጊዜ ገደብ ወደ 45 ቀናት መራዘሙ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ በአየር ተጓጉዘው አገር ውስጥ ለሚደርሱ ዕቃዎች ለነፃ ዝውውር እንዲለቀቁ የተደነገገው የ10 ቀናት የጊዜ ገደብም ወደ 30 ቀናት ሲራዘም እነዚህ ለውጦች ነጋዴዎች የጉምሩክ ሥነ ሥርዓቶችን በተሻለ ሁኔታ እንዲያጠናቅቁ፣ ዕቃዎቻቸውን በወቅቱ እንዲያስለቅቁ አዋጁ ጉልህ ሚና አለው ተብሏል።