ኢትዮጵያና ኬንያ ንግድና ባህልን በመጋራት፣ በንጹህ ሀይል፣ በመንገድ ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ያላቸውን ነባር ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት በኬንያ በዛሬው እለት በተከበረው የማሹጃ ቀን ወይም የጀግኖች ቀን ብሔራዊ በዓል ላይ በክብር እንግድነት በመታደም ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
የኬንያ የጀግንነትና የመስዋዕትነት ታሪክ፤ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር ይመሳሰላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እነዚህ የጋራ ታሪኮች ነጻነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በመስዋዕትነት የተረጋገጠ መሆኑን ያስገነዝቡናል ብለዋል።
ብሔራዊ በዓሉ ለኬንያ ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና ልማት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ጀግኖች ክብር የሚሰጥበት ቀን መሆኑን ተነግሯል፡፡
