የውጭ አገር ባለሀብቶች እና ተቋማት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ውስጥ በመግባት እንደ አክሲዮን፣ ቦንድ እና የጋራ መዋጮ ፈንዶች ያሉ የፋይናንስ ሰነዶችን መግዛት የሚያስችላቸው ረቂቅ ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በረቂቅ ደንብ ዙሪያ የተዘጋጀ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት መድረክ በተመለከተ ይፋ ባደረገው መረጃ በዚህ የውጭ ፖርትፎሊዮ ኢንቨስትመንት መሳተፍ የሚችሉት የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውንም አስፍሯል፡፡
ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መስተናገድ የሚፈልግ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ሀገር ዜጋ እንደ የውጭ ፖርትፎሊዮ ኢንቨስተር ኢንቨስት ለማድረግ ብቁ እንደማይሆንም አስፍሯል፡፡
በዘርፉ ለመሰማራት የሚያመለክቱ አካላት የኢንቨስትመንት ካፒታሉን ሕጋዊ ምንጭ ለማረጋገጥ በቂ የሆነ የተረጋገጠ የገንዘብ ምንጭ ማስረጃ ማቅረብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕግና በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች ማዕቀብ ያልተጣለባቸው መሆን እንዳለባቸውም በረቂቅ ደንቡ ሰፍሯል፡፡
በመጪው ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም በሚካሄደው የውይይት መድረክ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ማንኛውም ፍላጎት ያላቸው ተሳታፊዎች በመገኘት በረቂቅ ደንቡ ላይ አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉም ጥሪ ቀርቧል።
