EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ 70 ግራም ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከዳቦ አምራች ማህበራት ጋር ስምምነት መደረሱን አስታወቀ።

ቢሮው ይሄን ያለው ከዳቦ አምራቾች ማህበር አመራሮችና አባላት ጋር በዳቦ አቅርቦት ዙሪያ በተወያየበት መድረክ ላይ ነው።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በከተማዋ የሚገኙ የዳቦ አምራቾች የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ በማድረግ 70 ግራም ዳቦ በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የድርሻቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ኃላፊዋ የከተማ አስተዳደሩ በመዲናዋ በቂ የስንዴ ዱቄት አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልፀው የዳቦ አምራቾች ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ ሠራተኞች ሲያጋጥሙ በ8588 ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀው በጥቆማው መሠረት ፈጣንና ተገቢ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በመጨረሻም የዳቦ አምራች ማህበራት አመራሮችና አባላት የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ታሳቢ በማድረግ 70 ግራም ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ይህንንም ለከተማ አስተዳዳሩ በአጭር ጊዜ ለማሳወቅ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።