EthiopiaNews

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ዋሽንግተን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ግጭት ለመቋጨት በመጪው ህዳር መጀመሪያ ላይ አዲስ የሦስትዮሽ የሰላም ድርድር በአቡ ዳቢ  እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

ዊትኮፍ በማህበራዊ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፤ በመጪው የፈረንጆቹ ኅዳር 10 እና 11 ቀን በአቡ ዳቢ የሚካሄደው ይኸው ውይይት ከጦርነት በኋላ ባሉ የደህንነት ዝግጅቶች፣ በሰብአዊ ጥረቶች እና ለዘላቂ ሰላም በሚወሰዱ በቀጣይ እርምጃዎች ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

በዚሁ በአቡ ዳቢ በሚካሄደው ድርድር ላይ የአሜሪካን የልዑካን ቡድን ለመምራት ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እና የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር በጋራ እንደሚሳተፉ ከአሜሪካ ባለስልጣናት በተገኘው መረጃ መረጋገጡን ኤክሲዮስ ዘግቧል።

የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ሳምንት በብራስልስ ከተማ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከብሪታንያ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከኔቶ ተወካዮች ጋር በመገናኘት ለዩክሬን ስለሚሰጡ የደህንነት ዋስትናዎች እና ከጦርነት በኋላ ስለሚኖረው የአውሮፓ የደህንነት መዋቅር እንደሚመክሩ ተገልጿል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ለድርድር ዝግጁ መሆኗን በተደጋጋሚ ቢገልጹም፤ ኪየቭ በድጋሚ እንድትደራጅ እና እንድትታጠቅ ብቻ የሚረዳ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን ግን እንደማይቀበሉ  አስታውቀዋል።