EthiopiaNews

የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ሊካሄድ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት ዋሽንግተን በሆርሙዝ ባህረ ሰላጤ በሚገኘው የኢራን ይዞታ ወታደራዊ ጥቃቶችን መሰንዘሯ  ታውቋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደገለጹት፤ ይህ የተፈጸመው የአየር ጥቃት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል በአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን ላይ የከፈተውን ተኩስ ተከትሎ የተሰነዘረ የአጸፋ እርምጃ ነው ተብሏል።

የኢራን መንግስት የዜና ወኪል ኢርና በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ዕለት ቀሽም በተባለው የኢራን ደሴት ላይ በርካታ ከፍተኛ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ግን ከአደራዳሪዎች ጋር የሰላም ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ዋዜማ በሰጡት መግለጫ በኢራን ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንደማይቸኩሉ እና ሀገሪቱን በኢኮኖሚ ማዳከማቸውን እንደሚመርጡ ቢገልጹም፤ የኢራንን የኑክሌር ፕሮግራም ጣቢያ ግን በአንድ ሰዓት ውስጥ ማውደም እንደሚቻል ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ይህ ወታደራዊ እርምጃ የተወሰደው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፓርቲያቸው ውስጥ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ግፊት እየተደረገባቸው ባለበት እና የአጋማሽ ዘመን ምርጫው የሪፐብሊካን ወይም የዲሞክራት ፓርቲ የኮንግረሱን የበላይነት እንደሚወስን በሚጠበቅበት ምዕራፍ ላይ ነው።