አሜሪካዊያን የትራምፕን የሁለተኛ የስልጣን ዘመን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመታት አፈጻጸም የሚገመግሙበትና የኮንግረስ የበላይነትን የሚወስነው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዛሬ ማክሰኞ መካሄድ ጀምሯል።
የተለያዩ የሕዝብ አስተያየት ጥናቶች እና ገለልተኛ ተንታኞች እንደሚያመለክቱት ዲሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ከሪፐብሊካኖች ይነጥቃሉ የሚለው ግምት ጎልቷል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በስልጣን ላይ ያለው ፕሬዝዳንት ፓርቲ በአጋማሽ ዘመን ምርጫ መቀመጫዎችን የማጣት ታሪክ ያለው ሲሆን፤ የትራምፕ ተቀባይነትም ከኢራን ጦርነት እና ከነዳጅ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው የተባለው።
ዲሞክራቶች በምክር ቤቶቹ አብላጫ ወንበር ለማግኘት ሦስት የሕዝብ ተወካዮች እና አራት የሴኔት መቀመጫዎችን ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ አብላጫነቱን ካገኙ በትራምፕ አስተዳደር ላይ ምርመራዎችን የመክፈት መብት ይኖራቸዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ደጋፊዎቻቸው ለሪፐብሊካን ዕጩዎች ድምፅ እንዲሰጡ የጠየቁ ሲሆን፤ የዲሞክራት ፓርቲ ዕጩዎችን እጅግ አደገኞች እና ጽንፈኞች ሲሉ በምርጫው ዋዜማ ላይ ከሰዋቸዋል።
