ኢትዮጵያ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ዓመት ድረስ 41 ሚሊየን ዜጎችን የአይን ጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የሁለት ሚሊየን ዶላር እቅድ ይፋ ማድረጓ ተገለጸ።
ይህ ኢንቨስትመንት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሺህ 200 በሚበልጡ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ውስጥ ጥራት ያለው የአይን ህክምናን ለማጠናከር፣ የመነጽር አቅርቦትን ለማስፋፋት፣ የቅድመ-ምርመራ እና የሪፈራል ስርዓትን ለማሻሻል እንዲሁም የዓይን ሞራ ህመም ቀዶ ህክምና ጥራትና ውጤትን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።
ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በእድሜ፣ በፆታ፣ በገቢ፣ በዓይን ሞራ ህመም ወይም በመኖሪያ ቦታ ሳይወሰን ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የአይን ህክምና እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑንም የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ይህ የተባለው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የአይን ጤና ጉባኤ በአንቲጓዋ እና ባርቡዳ ሴንት ጆንስ ከተማ በተካሄደበት ስነ ስርዐት ላይ ሲሆን በመድረኩ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የአይን ጤና አገልግሎትን ከሀገሪቱ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ጋር በማቀናጀት ላከናወነችው ሥራ ግሎባል ቪዥን ኢምፓክት አዋርድ የተሰኘ ሽልማት እንደተበረከተላት ተመልክቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1.1 ቢሊየን የሚበልጡ ሰዎች በቅድመ መከላከል ወይም በሕክምና ሊድኑ የሚችሉ የእይታ ማጣት ችግር እንደሚገጥማቸው እና ከ2 ቢሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ የእይታ እክሎች እንዳሉባቸውም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
