የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የፈጠሩ 100 ሴቶች ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታወቀ፡፡
ይህ እውቅና በአፍሪካ ሃይፐርስኬለርስ እና ዘ-ሊትልስቴፕስ ግሩፕ በተሰኙ አህጉር አቀፍ ተቋማት የተበረከተ ሲሆን ሚኒስትሯ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ በነበሩበት ወቅት የዲጂታል መሰረተ ልማት በማስፋፋት፣ በዲጂታል ፋይናንሲንግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን በማድረግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው እውቅና የተሰጣቸው ተብሏል።
እውቅናው በአፍሪካ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የክላውድ፣ የዳታ ማዕከላት፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ዘርፎች ፈጠራንና የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታን በመምራት ላይ ለሚገኙ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች የተሰጠ መሆኑን ተጠቁሟል።
በአፍሪካ ሃይፐርስኬለርስ መረጃ መሰረት ከምሥራቅ አፍሪካ ከተመረጡ ግንባር ቀደም ሴት መሪዎች መካከል የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለነበሩት ፍሬሕይወት ታምሩ ከኤምቲኤን፣ ማይክሮሶፍትና ከሌሎች ተቋማት መሪዎች ጋር ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።
