EthiopiaNews

በትግራይ ክልል በድርቅ እና በግጭት ለተጎዱ ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም መልሶ ለማቋቋም የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር ገለጸ፡፡

የክልሉ አስተዳደርና የህዝብ አገልግሎት ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ አሰፋ አብርሃ ይህንን ያሉት የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር አመራሮች ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች፣ አምባሳደሮች እና አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በትላንትናው ዕለት ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ባለአደራ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች ዙሪያ ከልዑካኑ ጋር የተወያየ ሲሆን በዚህ ወቅትም የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ግንባታ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና መልሶ የማቋቋም ሂደት እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን በማስፈን ረገድ ጥሩ ሥራ መሠራቱን አሰፋ አብርሃ ገልጸዋል።

እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ተሃድሶ ማዕከላት ለመግባት መመዝገባቸውን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው እነዚህን ሰዎች ለማሰልጠን እና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ ለመቀላቀል ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመቀሌ ከተማ የሚኖረው ህዝብ ውስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጸው ከግጭቱ በተጨማሪ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም እና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ድጋፍ እንዲደረግም ነው የጠየቁት፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ኦዞኒያ ኦጂኤሎ በበኩላቸው በሰላም ማስከበር፣ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ የደራሽ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት በትላንትናው ዕለት መቀሌ የገቡት የልዑካን ቡድኖቹ በከተማዋ ከሚገኙ ከሃይማኖት አባቶች ጋርም ተወያይተዋል፡፡