ከ100 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ባላት ሀገር ከ10 ሺህ በታች ግብር ከፋዮች ገቢ የሕዝቡን ፍላጎት ማሟላት እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ግብር የሚከፍሉ አካላት በጣም ጥቂት መሆናቸውን በመግለጽ የግብር መሠረትን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 454 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቦ 458 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ከሞላ ጎደል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጨማሪ ብድር ሳይጠየቅ ወጪን በገቢ ልክ ለማድረግ እንደተሞከረ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከወጪው ውስጥ 88 ቢሊየን ብር ገደማ ለዕዳ ክፍያ መዋሉን አመልክተዋል።
ሰዎች ከሚሠሩት ሥራ በየደረጃው መጠነኛ ግብር መክፈል ካልቻሉ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብር መክፈል ክብርና ኩራት መሆኑን አመልክተው የግብር ስወራን መቆጣጠርና ታማኝ ግብር ከፋዮችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
