News

አዲስ ነገር – ዩኤኢ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ዙሪያ እና ሌሎችም አጫጭር መረጃዎች

👉🏾 የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በታላቁ የህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ የሚደርጉትን ድርድር እንደምትደግፍ አስታወቀች፡፡ ሶስቱ አገራት አለመግባባታቸውን በማጥበብ ለህዝቦቻቸው የሚጠቅም ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ጥሪውን ያቀረበው መግለጫው ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት መደረጉ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው የህብረቱ መሪ ሀሳብን የሚደግፍና የሚያበረታታ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

👉🏾 የአልቃይዳውን መሪ አይመን አልዛዋሂሪን የገደለችው ዩ ኤስ አሜሪካ ዜጎችዋ ራሳቸውን ከበቀል ጥቃት እንዲጠብቁ አስጠነቀቀች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአልዛዋሂሪ መገደል ያበሳጫቸው ተከታዮቹ በማንኛውም ሰዓት እና ቦታ ተቃውሞ ሊያስነሱና አሜሪካዊያንን የጥቃት ኢላማቸው ሊያደርጉ ስለሚችሉ በየትኛውም አገር ያሉ አሜሪካውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

👉🏾 በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ያደረጋቸውን ውይይቶች ተከትሎ ምርመራ ለማድረግ ፈቃድ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ተመድ አስታውቋል፡፡ የባለሙያዎቹ ቡድን በኢትዮጵያ ያደረገውን የ5 ቀናት ጉብኝት አጠናቆ ሲመለስ ባወጣው መረጃ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝቶ መመክሩ ተጠቁሟል፡፡ በውይይቶቹ ላይ ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተባብሮ በሚሰራባቸው መንገዶች እና የኮሚሽኑ ተግባርና ሃላፊነት ዙሪያ ንግግር መደረጉ የተነገረ ሲሆን ቡድኑ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችለውን ፈቃድ በተመለከተ ጥያቄ ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከኮሚሽኑ ጋር በዝርዝር የእንቅስቃሴ ማዕቀፎች ላይ መግባባት ላይ ከተደረሰ አብሮ የመስራትን ጉዳይ መልሶ የማጤን እድል እንዳለ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

👉🏾 የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ:- ከሳምንት በኋላ ለሚደረገው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድንን የሚመሩት የቀድሞ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ርዕሰ ብሔር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለዚሁ ተልዕኮ ሲባል የኬንያ ርዕሰ ከተማ ናይሮቢ መግባታቸውን የኢጋድ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እስከ ምርጫው መዳረሻ ባለው ጊዜ ከተለያዩ የኬንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ተገናኝተው በምርጫው ጉዳይ ላይ እንደሚወያዩ መረጃው አክሎ ገልጿል፡፡ በነገራችን ላይ ከእራሳቸው በተጨማሪ የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪኪዌቴ የኬንያውን ምርጫ የሚታዘበውን የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ቡድንን እንደሚመሩ ተነግሯል፡፡

👉🏾 ይህን ያውቃሉ?
በኢትዮጵያ ኢንተርኔትን ለመጠቀም የምናወጣው ወጭ ምን ያህል ነው?
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ዜጎች ኢንተርኔትን ለመጠቀም የሚያወጡት ወጪ ከገቢያቸው 2 በመቶውን ብቻ መሆን እንዳለበት ቢጠቁምም በኢትዮጵያ ያለው የመጠቀሚያ ዋጋ ግን ከ5 እስከ 7 በመቶ የሚደርስ መሆኑ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡

የኢቢኤስ የአዲስ ነገር / What’s New መረጃዎችን በሚከተሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይከታተሉ::

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New