ነፃ የአየር ሰአት ለፖለቲካ ፓርቲዎች
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት አጠቃቀም ቅዳሜ፣ እሁድ እና የበዓላት ቀናትን ሳይጨምር ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወን ተገልጿል።
የዘንድሮው ድልድል ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ብልጫ እንዳለው የተገለፀ ሲሆን ይህም በ50 መገናኛ ብዙሃን (በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በጋዜጣ) የሚስተናገድ ይሆናልም ነው የተባለው።
ቦርዱ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ ለፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት ድልድል ማድረግ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ይህ የነፃ የአየር ሰዓት ድልድል የሚካሄደውም ቦርዱ ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመሆን ባበለጸገው አዲስ ሲስተም መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ አሰራር የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ሀሳብ፣ ፖሊሲ እና ፕሮግራም ለመራጩ ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፤ ፓርቲዎች የሚመደብላቸውን ነፃ የአየር ሰዓት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ይህ ድልድል ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ናቸው።
