EthiopiaNews

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት

ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሳውቋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ያሳወቀው የ18 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አፈፃፀምን ዛሬ በገመገመበት መርሃ ግብር ላይ ሲሆን የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘገብ አስችሏታል ብሏል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ከተጀመረበት ካለፉት 8 ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ በአማካይ የ7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተናግሯል።

የገንዘብ ሚኒስቴርም በተመሳሳይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ከማሳደግ አኳያ ከፈረንጆቹ 2023 እስከ 2024 ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷን ጠቁሟል።

በተመሳሳይ ከ2024 እስከ 2025 መጨረሻ ድረስ ወደ 8 ነጥብ 33 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷን ያብራራው የገንዘብ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሀገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ እንዲሁም የውጭ ንግድ እንዲያድግና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።

የብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሀዝ ማውረድ መቻሉንና የኢኮኖሚ ማሻሻያው የማሕበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ጥብቅ ክትትል እየተደረገለት መሆኑን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN