EthiopiaNews

በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 18 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት የኢዜማው መሪ  እዮብ መሳፍንት በተወዳደሩበት የምርጫ ክልል ከፍተኛ ድምፅ ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ይህ የተባለው የኢትዮጵያ  ብሔራዊ  ምርጫ ቦርድ ትናንት   ምሽቱን በሰጠው መግለጫ  የፀደቁ  የምርጫ ክልል ውጤቶችን ይፋ ሲያደርግ ነው።

ቦርዱ በዚህ መግለጫው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፣ቤንሻንጉል፣ኦሮሚያ፣ድሬደዋ፣እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ካሉ  የምርጫ ክልሎች የመጡና የፀደቁ ውጤቶችን ነው ይፋ ያደረገው።

በዚሁ መግለጫ  ከ1ሺህ139 የምርጫ ክልሎች ውስጥ የ1ሺህ 131 ውጤት ተጠቃሎ ለቦርዱ መድረሱ የተነገረ  ሲሆን የ7ቱ ምርጫ ክልሎች ውጤት አልደረሰም ነው የተባለው ።

ከነዚህ የምርጫ ክልሎች ውስጥ 6ቱ በሱማሌ ክልል አንዱ በአማራ ክልል የሚገኝ ነውም ተብሏል።

በትናንቱ መግለጫ ላይ 120 የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታ መቅረቡንና የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ እነዚህ ውጤቶች እስካልተጣሩ ግዜ ድረስ ጥቅል ውጤቱ እንደማይገለፅ ነው የተናገሩት።

አንዳንድ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን በመያዝ አሸንፈናል የሚሉ መግለጫዎችን እያወጡ መሆናቸውን ተከትሎም ህብረተሰቡ ትክክለኛውን ውጤት ከምርጫ ቦርድ ብቻ መጠበቅ እንደሚገባው ቦርዱ አሳስቧል።

ውጤት የማዳመር እንዲሁም ኦዲት የማድረግ ስራዎች ከጠዋት እስከ ምሽት እየተሰሩ ነው ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ሀይሉ ቅሬታ የቀረበባቸው 120 የምርጫ ክልሎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ስራም በህግ ባለሙያዎች ታግዞ እየተካሄደ መሆኑን አሳውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቦርዱ በትናንትናው እለት የውጤት ማረጋገጥና የኦዲት ሂደቱን ለጋዜጠኞች በዝርዝር ያስመለከተበትን ገለፃም አድርጓል። ዘገባው የሪፖርተራችን አቤል አበበ ነው።

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews