EthiopiaNews

የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ስለ ቤት ኪራይ ዋጋ

አከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ብቻ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የአከራይና ተከራይ ግንኙነትን በቴክኖሎጂ ለማዘመንና በዘርፉ የሚታዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የዲጂታል ምዝገባ ሂደት መጀመሩን የገለፀ ሲሆን እስካሁን ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ወደሲስተሙ መግባታቸው ተገልጿል።

ይህ አዲስ አሰራር በቤት ኪራይ ዋጋ ላይ ያለ አግባብና ያለምንም ምክንያታዊ መነሻ ይደረግ የነበረውን ያልተገባ ጭማሪ ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ሲባል ወደ ዲጂታል ቋቱ የገቡት እነዚህ የኪራይ ቤቶች በየትኛው ክፍለ ከተማ፣ ወረዳና ብሎክ ላይ እንደሚገኙ ሙሉ መረጃቸው በግልጽ የሚታወቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል ነው የተባለው።

ይህም አከራዮች ቤታቸውን ስለማከራየታቸው መረጃ የመደበቅ ዕድል እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው የተባለ ሲሆን በአዲሱ አሰራር መሠረት አከራዮች በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት ብቻ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር እንደማይችሉ ተገልጿል።

መንግሥት በየዓመቱ አንድ ጊዜ የከተማዋን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የገበያ ጥናት ካካሄደ በኋላ፣ የገበያ ዕድገት መኖሩ ሲረጋገጥ በየዓመቱ ሰኔ 30 ላይ በሚያወጣው ይፋዊ መግለጫ መሠረት የዋጋ ጭማሪውን በፐርሰንት ይወስናል ነው የተባለው።

ከዚህ ውጭ የተጋነነ ዋጋ የሚጨመርበት ምንም ዓይነት አሰራር እንደማይኖር አስገንዝበዋል።