Sports

EBS SPORT – እለታዊ መረጃዎች

  • በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈፅሞ ያልተጠበቀ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ለአይቮሪኮስት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመክፈቻ ጨዋታቸውን በማላዊ ተረተው የጀመሩት ዋልያዎቹ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ግብፅ ጋር አድርገው ከአመርቂ የጨዋታ ብልጫ ጋር የ 2 ለ 0 ድልን አስመዝግበዋል፡፡ በካፍ እገዳ ምክንያት የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጪ በቢንጉ ለማድረግ በተገደዱበት የምሽቱ ጨዋታ ግቦቹን ዳዋ ሁቴሳ እና ሽመልስ በቀለ ከእረፍት በፊት ከመረብ አሳርፈዋል፡፡   1
  • ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሁለት ሚሊየን ብር ሽልማት ለመስጠት ቃል ተገብቶለታል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ለዋልያዎቹ የገንዘብ ሽልማቱን ቃል የገባው የትናንት ምሽቱ ድል ተከትሎ ነው፡፡ የፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ባስተላለፉት መልዕክት “ይህ ከእግር ኳስ በላይ ብዙ ትርጉም ያለውን ጨዋታ በድል በማጠናቀቃችሁ ኩራት ተሰምቶናል። ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጋር በአስቸኳይ ተነጋግረን ለዛሬው ድል እና ባለፈው ጨዋታ ላደረጋችሁት ሁሉ ሁለት ሚልየን ብር ሽልማት ለቡድኑ አባላት እናበረክታለን።” ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡   2
  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ምድቡን በበላይነት እየመራ ይገኛል፡፡ በምድብ አራት ከማላዊ፣ ግብጽ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው ብሔራዊ ቡድኑ ከሁለት ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ ሶስት ነጥቦች አኝግቷል፡፡ ውጤቱን ተከትሎም ምድቡን በግብ ክፍያ ብልጫ የሚመራበትን እድል አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ጊኒ እና ማላዊ ባደረጉት ሌላ ጨዋታ ጊኒ በናቢ ኬታ ብቸኛ ግብ ጨዋታውን 1 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች። እናም አሁን ላይ ሁሉም ቡድኖች ሶስት ሶስት ነጥቦች በያዙበት ምድብ ከኢትዮጵያ በመቀጠል ማላዊ፣ ጊኒ እና ግብጽ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል፡፡ ቡድኑ የምድቡን 3ኛ ጨዋታ በወርሃ መስከረም በኮናክሪ ከጊኒ አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡   3
  • የሃሙስ ምሽቱ የአፍሪካ ማጣሪያ ውጤት በግብፆቹ ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡ በዋልያው የ 2 ለ 0 ሽንፈት የደረሰባቸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቀናቃኝ የሆኑት ፈርኦኖቹ በተለያየ መንገድ በሃገራቸው ብሔራዊ ቡድን አቋም ቅሬታና ድንጋጤያቸውን ሲያሰሙም ታይተዋል፡፡ የግብጹ እጅጉን ተፈላጊ ጋዜጣ አል አህራም ውጤቱን አስደንጋጭ ሲለው የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች እንቅስቃሴም እጅጉን ደካማ ሲል ገልፆታል፡፡ ተመሳሳይ አገላለፆችን ሲጠቀም የታየው ዴይሊ ኢጅፕት በበኩሉ ውጤቱን አስደንጋጭ ሲል ገልፆ ትችቱን አዝንቧል፡፡  የግብጽ መገናኛ ብዙሀንም ሆኑ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ የሆኑ ግብጻውያን መረር ያለ ትችትን ከአስደንጋጩ ሽንፈት መልስ ሲያሰሙም ታይተዋል፡፡    4
  • በሴካፋ ዋንጫ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከፍጻሜው ውጪ ሆኗል፡፡ በግማሽ ፍፃሜ ከኡጋንዳ ጋር የተጫወቱት ሉሲዎቹ 120 ደቂቃ በፈጀው ፍልሚያ 1 ለ 0 ተረተው ከፍጻሜው ለመቅረት ተገደዋል፡፡ የትናንት ቀትሩን ውጤት ተከትሎም የሉሲዎቹ ተጋጣሚ የነበረችው የውድድሩ አስተናጋጅ ኡጋንዳ ወደ ፍፃሜ ለማለፍ ችላለች፡፡ በሌላ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ታንዛኒያ እና ብሩንዲ ጋር ተገናኝተው ጨዋታው በብሩንዲ 2-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል፡፡ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹን ውጤት ተከትሎም በእለተ ቅዳሜ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ የውድድሩን ዋንጫ ከፍ ለማድረግ በ9 ሰዓት የሚፋለሙ ይሆናል። ተሸናፊዎቹ ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በበኩላቸው ከፍፃው ጨዋታ ቀደም ብሎ በ6 ሰዓት የደረጃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡  5
  • ማንችስተር ዩናይትድ አንቶኒን ለማስፈረም በሚያደርገው ጥረት መልካም ሂደት ውስጥ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡ የላንክሻየሩ ተወካይ የአያክሱን የክንፍ ስፍራ ተጫዋች ለማስፈረም ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከዛ ጋር ተያይዞም 51 ሚሊየን ፓውንድ የሚገመተውን ብራዚላዊ በተመለከተ ወኪሎቹ ከእንግሊዙ ክለብ ጋር ንግግር እያደረጉ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ቀጣይ ሁኔታ በመጪው ቀናት ቁርጡን በሚለየው ተጫዋች ዙሪያም ማንችስተር ዩናይትድ መልካም የሚባል የዝውውር ሂደት ውስጥ እንደሚገኝ እየተገለጸ ይገኛል፡፡       6
  • የአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች የራሂም ስተርሊንግን ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት እየተከታተሉ መሆናቸው ይሰማል፡፡ በተለይም እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች በመጪው ክረምት ከማንችስተር ሲቲ ሊለቅ እንደሚችል በብዙ ክለቦች ዘንድ መገመቱ ትኩረታቸውን በስተርሊንግ ላይ እንዲያደርጉ ምክንያት ተደርጎም ይቀርባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በሲቲ በኩል ተጫዋቹን በ2023 በነጻ ዝውውር የማጣት እድል ያለ መሆኑን ተከትሎ በመጪው ክረምት ተጫዋቹን ሊሸጠው እንደሚችል ይበልጥ እንዲገመት አድርጎታል፡፡ ስተርሊንግን ከሚፈልጉ ክለቦች መሀከልም በቀዳሚነት ስሙ የሰፈረው የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ ነው፡፡     7
  • ሊቨርፑል ዳርዊን ኑኔዝን በእጁ ለማስገባት መቃረቡ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ የቤኔፊካው የፊት መስር ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 34 ግቦችን ያስቆጠረ ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ኮከብ ነው፡፡ ያንን ተከትሎም ከሊቨርፑል እንደሚለቅ የሚጠበቀውን ሳዲዮ ማኔን ለመተካት በሚል ሊቨርፑል ከሰሞኑ ተጫዋቹን ለማስፈረም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ እየወጡ እንዳሉ መረጃዎች ከሆነም የአንፊልዱ ክለብ ኑኔዝን በእጁ ለማስገባት መቃረቡ ታውቋል፡፡ ሊቨርፑል ለተጫዋቹ ዝውውር በሂደት ወደ 85 ሚሊየን ፓውንድ ሊያድግ የሚችል የ68 ሚሊየን ፓውንድ ክፍያ ለመፈፀም መስማማቱም ተይይዞ ተጠቅሷል፡፡    8
  • የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሴንት ጀርሜየን በመጪዎቹ ቀናቶች ማውሪሲዮ ፖቼቲንሆን አሰናብቶ አዲስ አሰልጣኝ እንደሚሾም ማርካ አስነብቧል፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ለፓሪሲያኖቹን የመሩት አርጀንቲናዊው በፓርክ ደፕሪንስ ያልተሳኩ ጊዚያትን ማሳለፋቸውን ተከትሎ የፈረንሳዩን ክለብ ሊለቁ የተቃረቡ ሲሆን እርሳቸውን በመተካትም ዚነዲን ዚዳን አዲሱ የፔይዤ አሰልጣኝ ሊሆን በእጅጉ ተቃርቧል፡፡ ክለቡ ከዚህ ቀደም ስፖርቲንግ ዳይሬክተሩን ሊዮናርዶን አሰንብቶ ሊዊስ ካምፖስን መሾሙ ይታወሳል፡፡ 9

የኢቢኤስ የአዲስ ነገር / What’s New መረጃዎችን በሚከተሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይከታተሉ::

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New