EthiopiaNews

ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና

የጤና ሚኒስቴር ለ175 የልብ ህሙማን ህጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አስታውቋል።

የመግባቢያ ሰነዱ በጤና ሚኒስቴር እና የልብ ቀዶ ህክምና አጋር በሆኑ የግል እና የመንግስት ሆስፒታሎች የተፈረመ ሲሆን፤ ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ዘመቻው ከሚያዝያ 12 ጀምሮ ለ45 ቀናት በግል እና በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጥ ይሆናል።

የመግባቢያ ሰነዱን ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙት የኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ፣ የኢትዮጵያ የልብ ማህበር፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የቅዱስ ዼጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል፣ የኤልውዘር የልብ ህክምና ማዕከል እና የኢትዮጵያ የህጻናት የልብ ማዕከል ናቸው።

የልብ ቀዶ ህክምና ዘመቻው በዘርፉ ያለውን ጫና ለማቃለል የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት በትብብር ሲሰሩ ዘለቄታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልፀው፣ የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙ አካላትን አመስግነዋል፡፡

ለነፃ የልብ ህክምና ዘመቻ የሚውለው ግብዓት በኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ ድርጅት የሚቀርብ ይሆናል።

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለ20 የልብ ህሙማን ህጻናት ህክምናው የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም በአጠቃላይ አገልግሎቱን የሚያገኙ ህጻናት ቁጥርን ወደ 195 ከፍ ያደርጋል፡፡

መረጃው ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ ነው።

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
https://ebstv.tv/