News

አዲስ ነገር – ኢራን ከአሜሪካ ጋር የእስረኞች ልውውጥ እና ሌሎችም መረጃዎች

🇨🇳 #ቻይና
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ሃገራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ንቁ ተዋናይ መሆን እንዳለባት ተናገሩ፡፡ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ይህንን ያሉት ለ7 አመታት ባላንጣ የነበሩትን ኢራን እና ሳዑዲ አረቢያን ስኬታማ በተባለ መንገድ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ አሁን ያለው የዓለም ስርአት የአዳጊ ሃገራትን ፍላጎት የማያስከብር በመሆኑ ለውጥ እንደሚሻ ገልፀው በተለይም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በአስቸኳይ ለውጥ ከሚያሻቸው ተቋማት አንዱ መሆኑን አስተያየታቸው ሰጥተዋል፡፡
ሺ ፒንግ በገዥው የኮሚኒስት ፓርቲ ለ3ኛ ጊዜ ለ5 አመታት በሥልጣን እንዲቆዩ ይሁንታ ማግኘታቸውን ተከትሎ አዳዲስ ሚኒስትሮችን መሾማቸውን ኤፒ በዘገባው አስታውሷል ።
🇮🇷 #ኢራን
ኢራን ከአሜሪካ ጋር የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች ።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ናስር ካናኒ ይሄንን የተናገሩት የእስረኞች ልውውጥን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሆነ ባስታወቁበት ጊዜ ነው፡፡
ቃል አቀባዩ ናስር ካናኒ እንደ ኢራን ሁሉ ከአሜሪካ ወገን ቀና ምላሽ ከተገኘ የእስረኞች ልውውጡ ወዲያውኑ ይጀመራል ብለው እንደሚያስቡ አናዶሉ ዘግቧል ።
በተያያዘ የኢራን አንድ ባለሥልጣን ከአሜሪካ ጋር በእስረኞች ልውውጥ ዙሪያ ከስምምነት ደርሰናል በሚል ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት ምላሽ ፈፅሞ ሃሰት ነው ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስተባበሉ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
🇲🇬 #ማዳጋስካር
በማዳጋስካር ስደተኞችን ጭና የነበረች አንድ ጀልባ በገጠማት የመስጠም አደጋ በትንሹ 22 ተሳፋሪዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡
አርባ ሰባት ስደተኞችን ጭና ከማዳጋስካር በፈረንሳይ ቁጥጥር ሥር ወዳለችውና “ማዬቴ ” ወደ ተሰኘችው ደሴት ስታመራ የነበረችው ጀልባ በደረሰባት አደጋ በትንሹ 22 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ቀሪዎቹ 23 ተሳፋሪዎች በተደረገላቸው የነፍስ አድን ሥራ ማዳን ተችሏል ተብሏል፡፡
የፈረንሳይዋ የማዮቴ ደሴት ከማዳጋስካር 350 ኪሜትር ርቃ የምትገኝ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2021 ብቻ ወደ ደሴቷ ለመግባት የሞከሩ 6500 ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ሬዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል ።
🇸🇦 #ሳዑዲ አረቢያ
የሳዑዲ አረቢያው ግዙፉ የነዳጅ አምራቹ ኩባንያ “አርማኮ” በአንድ አመት ብቻ የ161.1 ቢሊየን ዶላር ትርፍ ማስመዝገቡ አነጋግሯል ።
አብላጫው ድርሻው በሃገሪቱ መንግስት ባለቤትነት ስር የሚተዳደረው አርማኮ ኩባንያ በአውሮፓውያኑ 2022 ያስመዘገበው የ161.1 ቢሊየን ዶላር ትርፍ በአውሮፓውያኑ 2021 ካስመዘገበው በ46 ነጥብ 5 ከመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑ ሲነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ ለትርፉ ማደግ በምክንያትነት ተነስቷል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በአርማኮ ኩባንያ ውስጥ 95 ከመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን ከኩባንያው የሚገኘው አብዛኛው ትርፍም ለመንግስት ገቢ እንደሚደረግ ቢቢሲ ዘግቧል ።
ግዙፉ የነዳጅ አምራች ኩባንያ አርማኮ ከአሜሪካው አፕል ኩባንያ በመቀጠል ቢሸጡ ግምታቸው ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን ከሚያስገኙ የዓለም ድርጅቶች መካከል ሁለተኛው መሆኑ ተነግሮለታል፡፡
ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New