EthiopiaNews

የራያ እና ፀለምት ተፈናቃዎች ጉዳይ

ከራያ እና ፀለምት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸዉን በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎችን ለመፍታት የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ አስታውቋል።

ብሔራዊ አቢይ ኮሚቴው በትላንትናው ዕለት ማለትም ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ስብሰባውን አካሂዷል።

አቢይ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባም ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራው እንዳይሳካ ከሁለቱም ክልሎች በኩል የማስተጓጎል ሚናን ሲጫወቱ የነበሩ አካላት እንደነበሩ ገምግሟል።

በተጨማሪም በአካባቢው በአስቸኳይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን ይህም አካባቢዎቹ ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ ወደ መደበኛው የአስተዳደራዊ ስርዓት እንዲመለሱ ያግዛል ሲል ብሔራዊ አቢይ ኮሚቴው በላከው መግለጫ ማስታወቁን የዘገበው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው።