የቅድመ ምክክር ገለጻ ለተመካካሪዎች
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚያካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሚሳተፉ ተመካካሪዎች የቅድመ ምክክር ገለጻ እየሰጠ ነው።
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት መኾኗን ገልጸዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን የአድዋን መንፈስ ሰንቀን ለሀገር ግንባታ ያዳበርነውን ወደ ምክክር እና መግባባት መቀየር ያስፈልገናልም ብለዋል።
ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የሚሰጠውን ገለጻ በአንክሮ በመከታተል ምክክሩን በስኬት ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል።
በገለጻው ወቅት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዓላማ፣ የውይይት ሂደት፣ የተመካካሪዎች ሚናና ኃላፊነት፣ እንዲሁም የውይይቱን ሥነ ምግባርና የአሠራር ሥርዓት በተመለከተ ማብራሪያ እየተሰጠ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ገለጻው ተመካካሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል መዘጋጀቱም ተገልጿል።
በገለጻው ላይ ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ ተመካካሪዎች መገኘታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
