EthiopiaNews

የቡናን ገቢ ስለማሳደግ


የግብርና ሚኒስቴር በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ከቡና ምርት ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ማቀዱን አሳወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ባሰናዳው ሀገራዊ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነድ ላይ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና ሽያጭ መገኘቱ በተነገረበት በዚህ መድረከ ላይ ከ2019 እስከ 2023 ዓ.ም ለአምስት ዓመታት በሚተገበረው በዚህ የቡና ልማት ፓኬጅ ይህንን ገቢ 6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል ተብሏል፡፡

ይህ የቡና ልማት ፓኬጅ ቡናን በመስኖ በማምረት፣ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያን በመጠቀም እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ዘዴዎችን በመተግበር አሁን ላይ በሄክታር የሚገኘውን 9 ኩንታል የቡና ምርት ወደ 21 ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱም ተነግሯል፡፡

የቡና ምርታማነትን ለማሳደግም በሚሰሩ ተከታታይ ስራዎች በ2023 ዓ.ም በኢትዮጵያ በቡና ምርት የተሸፈነውን የመሬት ስፋት ወደ 4 ሚሊዮን ሄክታር በማሳደግ ሀገሪቱ አሁን ላይ ከቡና ምርት የምታገኘውን 30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግም ታቅዷል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት የተነሱ ነጥቦች በሰነዱ ላይ ተካተውበት ሰነዱ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ መተግበር ይጀምራል ተብሏል ሲል የዘገበው ዘነበ ኃይሉ ነው፡፡