EthiopiaNews

የአፍሪካ የሉዓላዊ ፋይናንስ ፎረም

ኢትዮጵያ የዕዳ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመውን ሁለተኛውን የአፍሪካ የሉዓላዊ ፋይናንስ ፎረም እያስተናገደች መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአህጉሪቱ ያለውን የበጀት ምህዳር እና የዕዳ ዘላቂነት መፍትሄዎችን ለማምጣት ከአፍሪካ የተውጣጡ ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው ሁለተኛውን የአፍሪካ የሉዓላዊ ፋይናንስ ፎረም የበጀት ምህዳርን ማሳደግ እና የዕዳ ዘላቂነትን ማረጋገጥ በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት የሚካሄድ መሆኑም ተገልጿል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰመሬታ ሰዋሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እና ቀጣይነት ያላቸውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶችን ጨምሮ በተከታታይ በተከሰቱ ዓለም አቀፍ ቀውሶች ምክንያት በአፍሪካ እየታየ ስላለው የበጀት ተጋላጭነት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በአህጉሪቱ ያለው የውጭ ፋይናንስ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ገልጸው በአውሮፓውያኑ በ2010 ከነበረበት 44 በመቶ በ2024 ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማለቱንም ጠቁመዋል።

ይህም ማለት በአንድ ወቅት ከውጭ ዕዳ ግማሽ ያህሉን መሸፈን ይችል የነበረው መጠባበቂያ ክምችት አሁን ላይ ከአንድ ሦስተኛ በታች ብቻ የሚሸፍን መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በፎረሙ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የዕዳ አስተዳደር ቢሮዎች፣ የባለብዙ ወገን ተቋማት፣ የብድር ደረጃ መመዘኛ ኤጀንሲዎች እና ተቋማዊ ባለሀብቶች የተገኙ ሲሆን በፎረሙ ቆይታ ተሳታፊዎቹ እንደ ግሪን ቦንድ እና የዕዳ ለአየር ንብረት ልውውጥ ባሉ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ተግባራዊ መፍትሄዎችን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል።

#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv