🗳️ ርዕሰ ብሄር ታዬ አፅቀስላሴ ስለ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ምን አሉ?
- ምርጫው ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በመመዝገብ፣ ብቁ አስፈፃሚ ለመለመለውና ድምፅ አሰጣጥን እስከ ሌሊት ጭምር በትጋት ላካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከተመዘገበው ህዝብ ውስጥ ከ94 በመቶ በላይ ወጥቶ መምረጡ ትልቅ መልእክት አለው ብለዋል።
በንግግራቸው ምርጫው ህዝቡ ልዩነትን ከፀብ ከአንባጓሮ ልምምድ ውጪ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያለውን ፍላጎት ያሳየበት ነውም ብለዋል።
በሂደቱ ያሸነፉም ሆነ በንቃት የተሳተፉ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በሚገባ ለህዝብ ያደረሱበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ህዝቡ የሀገር ፍቅሩን በድምፅ መስጫ ካርዱ ያሳየበት መንገድ መሆኑንም አንስተዋል።
በካርዱ ይህን አይነት ትምህርት ለሰጠን የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ብቻ ሳይሆን አክብሮቴንም ለመስጠት እወዳለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።
እነዚህ ይፋ የተደረጉ ውጤቶች የአደራ ማህተም ናቸው፤ ያሉት ርዕሰ ብሄሩ ድምፅ ያገኙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ይህንን ሀላፊነት በተረዳ መልኩ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በምርጫው ያገኛችሁትን ተቀባይነት አደራችሁን በታማኝነት ለመፈፀም ልትጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
ከምርጫ ውጪ በሆነ መንገድ ስልጣን ለመያዝ ምኞት ያላቸው ወገኖች የፓለቲካ መንገዳቸውን ከዚሁ ስልጡን መንገድ ጋር ማስታረቅ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
የህዝብ ድምፅ ያልዳሰሰው ስልጣን መያዣ መንገድ ከዚህ ወዲህ በኢትዮጵያ ዝግ ስለሆነ ፈጥኖ ትክክለኛውን መስመር መያዝ ይገባልም ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
ይህን መንገድ ያልተቀበሉ ግን የኢትዮጵያ የፓለቲካ ድርሳን ሲፃፍ የግርጌ ማስታወሻ ከመሆን ያለፈ እጣ አይኖራቸውም ሲሉም ተናግረዋል።
ቦርዱም በዚህ ምርጫ ከገጠመው ፈተና በመማር የገጠሙትን ችግሮች የተሻለ ተቋም ለመገንባት እንዲጠቀምበት ሲያሳስቡ ስኬቶቹን ደግሞ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በመደምደሚያቸው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለምርጫ ታዛቢዎች፣ ለፀጥታ ሀይሎች፣ ለመገናኛ ብዙሀንና በሂደቱ ላይ ለተሳተፉ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም አካላት ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል።
