በትግራይ ክልል ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን ማስወጣቱን የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ማለትም ከአዲግራት፣ አክሱም፣ መቀሌ እና ራያ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሶስት ሳምንታት 10 ሺህ 144 ተማሪዎች ማስወጣቱን የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው ተማሪዎቹ ከሀምሌ 1 ጀምሮ የእረፍት ጊዜያቸው በመሆኑ ወደየአካባቢያቸው መሄድ ቢፈልጉም በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይችሉ መቆየታቸውን በመጠቆም ከፌደራልና ከአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም ከትራንስፖርት ማህበራት ጋር በመተባበር በሰመራ ዩኒቨርሲቲ በኩል መውጣታቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህም ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 335፣ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 992፣ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ 3 ሺህ 668 እንዲሁም ከራያ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 149 ተማሪዎችን በድምሩም 10 ሺህ 144 ተማሪዎችን እስከ ኮምቦልቻና አዲስ አበባ ድረስ ትራንስፖርት በማመቻቸት ማጓጓዝ መቻሉን ገልጿል፡፡
ተማሪዎቹ የነበራቸው የእረፍት ጊዜ በነበረው የጸጥታ መታወክ ችግር ምክንያት ለ1 ወር ያህል የባከነ በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ ተጨማሪ የእረፍት ጊዜ እንደሚኖራቸውና በዚህ የእረፍት ቆይታቸውም አገርአቀፍ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል ከአክሱም፣ ከአዲግራት እና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ለመመረቅ ያልተጠናቀቁ የትምህርት ተግባራት ያላችሁ ተማሪዎች ትምህርታችሁን የምታጠናቅቁበትና የምትመረቁበት ሁኔታ እንደሚመቻች እወቁልኝ ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስከዛው ድረስ በትዕግስት እንድትጠብቁን ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም ከተለያዩ ክልሎች በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የክረምት መርሀግብር የምትከታተሉና በጸጥታ ችግር ምክንያት መጓዝ ያልቻላችሁም በቀጣይ በሚቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ትምህርቱን ለመከታተል እድል ስለሚኖራችሁ እናተም በትእግስት እንድትጠብቁ ሲል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው ጨምሮ አመልክቷል፡

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 7696 ላይ ይላኩልን።

Join Our Telegram

Click Here To follow Us

ኢቢኤስ

EBS