LatestNewsSports

የኢቢኤስ ስፖርት ዜናዎች

– በፊፋ የሀገራት ደረጃ ኢትዮጵያ ከቀደመው ወር ተመሳሳይ ደረጃን አግኝታለች። ወርሀዊ የሀገራት ደረጃ ይፋ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ወር ያገኘውን ተመሳሳይ 137ኛ ደረጃን ይዟል። በሴካፋ ከ 23 ዓመት በታች ውድድር ደካማ እንቅስቃሴን ያሳየው ቡድኑ የደረጃ ለውጥ ሳያደርግ በተቀመጠበት ወርሀዊ ደረጃው ከአፍሪካ 40ኛ ሆኗል። ቤልጅየም አሁንም የሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ ስትችል ብራዚል እና ፈረንሳይ ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ተጋጣሚዎቹን ሀገራት በቀጣዮቹ ቀናት የሚውቅ ይሆናል፡፡ ለ 2021ዱ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ስነስርዓት በመጪው ሳምንት የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎም ዋልያዎቹን ጨምሮ 24ቱም ተሳታፊ ሀገራት ከማን ጋር እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡ ከስምንት አመታት ቆይታ በኋላ ለውድድሩ ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በቋት አራት ከማላዊ፣ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮሞሮስ እና ጋምቢያ ጋር በጋራ ተቀምጧል።

– ሊዮኔል መሲ በፒኤስጂ ቤት የመጀመሪያ ልምምዱን አድርጓል። ከረጅም አመታት የባርሴሎና ቆይታ በኋላ ወደፓሪስ ያመራው አርጀንቲናዊ ከአዲሱ ቡድን አባላት ጋር ትውውቅ ያደረገ ሲሆን የመጀመሪያ ልምምዱንም ከውኗል። በነፃ ዝውውር ፒኤስጂን የተቀላቀለው ሜሲ በመጀመሪያ ቀን ልምምዱ ቀለል ያሉ እንቅስቃሴዎችን በግሉና ከቡድኑ ጋር ሲሰራ ታይቷል።- ሊቨርፑል ተጨማሪ ተጫዋቾች የማስፈረም ፍላጎት እንደሌለው የርገን ክሎፕ ተናግረዋል። ሊቨርፑል በዘንድሮው ክረምት የአርቢ ሊፕዚንጉን ኢብራሂም ኮንቴ ከማስፈረሙ ውጪ በዝውውር ገበያው ሲሳተፍ አልታየም። ክሎፕ አሁን እንዳሉት ደግሞ ቡድናቸው በቀሩት የዝውውር ቀናት ተጫዋች የማስፈረም ምንም አይነት እቅድ እንደሌለው ገልፀዋል።

– ማንችስተር ሲቲ ለሀሪ ኬን 150 ሚሊየን ዩሮ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑ ተሰምቷል። ከሳምንት በፊት ጃክ ግሪሊሽን ያስፈረመው የኢትሀዱ ክለብ አሁን ደግሞ እንግሊዛዊውን አጥቂ በማንኛውም መንገድ በእጁ ለማስገባት ቆርጧል። ያንን ተከትሎም ሲቲ ለኬን ዝውውር 150 ሚሊየን ዩሮ ወይም 127 ሚሊየን ፓውንድ ለመክፈል መዘጋጀቱ ታውቋል።

– ሮሜሉ ሉካኩ በቼልሲ ቤት ቆይታው የማንችስተር ዩናይትድ ድክመቱን ማረም እንዳለበት ጋሪ ኔቭል ተናግሯል። በኢንተር ሚላን አስደናቂ ጊዜን ያሳለፈው ቤልጄማዊ አጥቂ ከዛ ቀደም ያላማረ የሁለት ዓመታት ቆይታን በኦልትራፎርድ ማሳለፉ ይታወሳል። ሉካኩ ዳግም ለቼልሲ በመፈረም ወደፕሪምየር ሊጉ መመለሱን ተከትሎም ያለፈ ድክመቱን ማረም እንዳለበት ኔቭል አሳስቧል።- ማርሴሎ ቤልሳ የሊድስ ውላቸውን አራዝመዋል። አርጀንቲናዊው አለቃ በኤላንድ ሮድ ለተጨማሪ አንድ አመት የሚያቆያቸውን የውል ስምምነት ተፈራርመዋል። ቤልሳ ቀድሞ እንደተገመተውም ቡድናቸው እሁድ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ከሚያደርገው የሊጉ መክፈቻ ጨዋታ በፊት የውል ማራዘሚያ ፊርማቸውን አኑረዋል።

– ኢንተር ሚላን ዴንዝል ዱምፍሪስን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል። የጣሊያኑ ክለብ ሆላንዳዊውን የመስመር ተከላካይ ለማስፈረም ከክለቡ ፒኤስቪ ጋር መስማማቱ ታውቋል። ደምፍሪስን በኤቨርተን ቢፈልገውም በመጨረሻ ግን በኢንተር ሚላን ተነጥቋል። በተያያዘ መረጃ ኤደን ዜኮ ሮማን በመልቀቅ በነፃ ዝውውር ኢንተርን መቀላቀሉ ይፋ ሆኗል።