ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ዛሬ ቃለ መሀላ ይፈፅማሉ

ዴሞክራቱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ዛሬ በነጩ ቤተመንግስት ቃለ መሀላ ይፈፅማሉ።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ የፖለቲካ መከፋፈል፣ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን በሀገሪቱ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ በሚገኝበት ወቅት ላይ በዓለ ሲመታቸው ይካሄዳል ተብሏል።

በዛሬው ዕለት የመጀመሪያዋ ጥቁር እስያዊት ሴት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት ካማላ ሃሪስም ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዋሽንግተን የሚገኘው የካፒቶል ሂል በዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች ጥቃት ከተፈፀመበት በኋላ በ50ዎቹ ግዛቶች ከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር እየተካሄደ ይገኛል።

ለጆ ባይደን በዓለ ሲመት ብቻም 25 ሺህ ወታደሮች የፀጥታ ቁጥጥር ለማድረግ በዋሽንግተን ተሰማርተዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምክንያት የጆ ባይደን በዓለ ሲመት ስነ ስርዓት እንደተለመደው በርካታ ህዝብ በተገኘበት እንደማይካሄድ ቢቢሲ በዘገባው ላይ አስፍሯል።

በዚህ በዓለ ሲመት ላይ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ባራክ ሁሴን ኦባማ ፣ ቢል ኪሊንተን እና ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ይሳተፋሉ ተብሏል።

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ በዓለ ሲመት ላይ እንደማይገኙ የተነገረ ሲሆን ተሰናባቹ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ግን በስነ ስርዓቱ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።