አዲስ ነገር – አጫጭር የዓለም መረጃዎች

🇮🇱#እስራኤል
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር እስራኤል በዌስት ባንክ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በትንሹ 11 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 102 የሚሆኑት ክፉኛ መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡
የሃማስ ታጣቂዎች ከጋዛ ወደ እስራኤል 6 ሮኬቶች ማስወንጨፋቸውን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ሌላ አዲስ የአየር ጥቃት መጀመሩን አልጀዚራ ዘግቧል።
🇬🇧#ብሪታንያ
ብሪታንያ ለ12 ሺ የጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ግዴታ የነበረውን የገፅ ለገፅ ቃለ መጠይቅ አሰራር ማስቀረቷን ይፋ አደረገች፡፡
ከአፍጋኒስታን፣ ኤርትራ ፣ ሊቢያ ፣ ሶሪያ እና የመን የመጡ 12ሺ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች የገፅ ለገፅ ቃለመጠይቅ ማድረግ ሳያስፈልጋቸው የብሪታንያ 10 ገፅ የዜግነት መጠይቅ ቅፅን በመሙላት ጉዳያቸውን ማስጨረስ ይችላሉ ተብሏል፡፡
አዲሱ አሰራር ይፋ የተደረገው የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አስተዳደር የጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገጥማቸውን የተንዛዛ አሰራሮችን ለመቀነስ በገቡት ቃል መሰረት አድርጎ ነው ተብሏል፡፡
የብሪታንያ የዜግነት ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለስልጣናት የቃለመጠይቅ አሰራሩ መቅረቱን ሲገልፁ ከዚህ ቀደም ሲተገበሩ የነበሩ ሌሎች አሰራሮች ግን ባሉበት የሚቀጥሉ ይሆናል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
#የአፍሪካ ቀንድ
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ወይም “ኢጋድ” በአፍሪካ ቀንድ ለ6ኛ ተከታታይ ጊዜ ዝናብ ላይጥል እንደሚችል አስጠነቀቀ ።
የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል በድርቅ በተጎዳው የአፍሪካ ቀንድ በቀጣዮቹ 3 ወራት ዝናብ ላይዘንብ እንደሚችል ትንበያውን ሲያስቀምጥ የድርቁ አደጋ በአውሮፓውያን 2011 ከደረሰው ቸነፈር የሚልቅ ሊሆን ይችላል ሲል በብርቱ አስጠንቅቋል።
የአፍሪካ ቀንድ አገራት 60 ከመቶ የሚሆነውን ዝናብ የሚያገኙት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ውስጥ ነው፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት “ፋኦ” በበኩሉ አዲስ ባወጣው ሪፖርቱ በአፍሪካ ቀንድ 23 ሚሊየን ህዝብ ለከፋ የምግብ እጥረት ተዳርጓል ሲል ማስታወቁን ዘ ኢስት አፍሪካን በዘገባው ተመልክቶታል ።
#ሶማሊላንድ
በራስ ገዟ ሶማሊላንድ በቀጠለው ግጭት በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ብቻ 150 ሰዎች ተገድለዋል ይላል የፍራንስ ትዌንቲ ፎር ዘገባ፡፡
የግጭቱ መነሻ በሶማሊላንድ የላስ ናኦድ ከተማ የጎሳ አባላት ተጠሪነታችን ለሶማሊያ መንግስት እንጂ ለሶማሊላንድ መንግስት አይደለም በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
ለሁለት ሳምንት በዘለቀው ግጭት 150 ሰዎች ሲገደሉ፣ 500 የሚሆኑት የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 185 ሺ ዜጐች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን በሪፖርቱ ያስታወቀው የመንግስታቱ ድርጅት ነው፡፡

የኢቢኤስ የአዲስ ነገር / What’s New መረጃዎችን በሚከተሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይከታተሉ::

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New