News

አዲስ ነገር – አጫጭር የዓለም መረጃዎች

🇪🇹 #ኢትዮጵያ
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን “ዩኤን ኤች ሲ አር” ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ በድርቅ ለተጐዱት ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለማቅረብ 137 ሚሊየን ዶላር እገዛ እንዲደረግለት ተማፀነ፡፡
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ የከፋ ነው በተባለው የምስራቅ አፍሪካው ድርቅ ለተጐዱት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ለሚገኙ ሰዎች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፎችን በአስቸኳይ ለማቅረብ ነው ለጋሽ አገራትን የፋይናንስ ድጋፍ የጠየቀው፡፡
ዩኤንች ሲ አር እንደሚለው በቀጣዮቹ 3 ወራት የሚጠበቀው ዝናብ በተፈለገው መጠን የማይዘንብ ከሆነ የሰብዓዊ ቀውሱ አደገኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ትንበያውን ማስቀመጡን ሪሊፍ ድረ-ገፅ ሃተታ ያሳያል፡፡
🇫🇷 #ፈረንሣይ
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአፍሪካ ግዳጅ ላይ ያሉ ወታደሮች ቁጥርን ለመቀነስ ቃል መግባታቸው ተሰምቷል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይህን ዕቅድ የተናገሩት በአፍሪካ የፓሪስ ተፅእኖ እየተዳከመ እና የሩሲያ እና የቻይና ተሰሚነት እየጐላ በመጣበት ጊዜ መሆኑ ነው የተነገረው ።
ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ “በአፍሪካ ያሉንን ወታደሮች በመቀነስ በተለይ ለአፍሪካ አገራት መንግስታት ወታደራዊ ሥልጠናና የጦር መሳሪያዎች በመደገፍ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፤” ብለዋል፡፡
ፈረንሳይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት 3ሺ ወታደሮች እንዳሏት የዘገበው ዘ ጋርዲያን ነው።
🇺🇸 #አሜሪካ
አሜሪካ ቲክ ቶክ የተሰኘዉ መተግበሪያ የመንግስት ተቋማቷ እንዳይጠቀሙ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።
የዋይት ኃውስ ባለስልጣናት ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቀው ከደህንነት ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሳው የቲክቶክ መተግበሪያን የፌዴራል የመንግስት ተቋሟት በሚቀጥለው 1 ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲያስወግዱ ታዘዋል።
የባይደን አስተዳደር እንደሚለው ቲክቶክ መተግበሪያ ቁልፍ የመንግሥት ሰነዶችን በመመንተፍ ላይ ያለ በመሆኑ ሁሉም የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት መተግበሪያውን እንዲያስወግዱ ጥብቅ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል ።
የአሜሪካ የመከላከያ ፣ የውጭ ጉዳይ እና የሃገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተቋሞቻቸው ቲክ ቶክ መተግበሪያን ጥቅም ላይ እንዳይውል ካደረጉ ጥቂት ተጠቃሽ ተቋማት መካከል መሆናቸውን ኤፒ ዘግቧል።
#ቱርክ
የዓለም ባንክ በቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት 34.2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ውድመት ማስከተሉን ይፋ አደረገ።
በቱርክ ርዕደ መሬት ወድሟል ተብሎ ከተመዘገበው 34.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ገሚሱ ህንፃዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ባንኩ ባወጣው አዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናቱ ባለፉት 3 ሳምንታት በቱርክ ባጋጠመው የርዕደ መሬት አደጋ የአገራዊ ጥቅል ምርቱን 4 ከመቶ ወይም 34.2 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሃብት ወድሟል ብሏል።
የቱርክ ምጣኔ ሃብት በአውሮፓውያኑ 2023 ያድጋል በሚል ካስቀመጠው የ4 ከመቶ እድገት በ0.5 ከመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ባንኩ መተንበዩን መኒ ዌብ ዘግቧል ።
የኢቢኤስ የአዲስ ነገር / What’s New መረጃዎችን በሚከተሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይከታተሉ::

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New