EthiopiaNews

የበጀት ግምገማ

በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የበጀት አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት የበጀት ፍላጎትን ገምግሟል።

ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በፅሁፍ የላኩለትን የ2018 የበጀት አፈፃፀምና የ2019 የበጀት ፍላጎት በገመገመበት መድረክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው የ2019 በጀት ዓመት የበጀት ፍላጎት ገንዘብ ሚኒስቴር ከሚፈቅደው የበጀት ጣሪያ በላይ መሆኑን በመግለፅ ጥያቄ አንስቷል።

በቋሚ ኮሚቴው ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለቀጣይ በጀት ዓመት የተጠየቀው በጀት በዚህ ዓመት ተፈፅመው ክፍያ ያልተፈጸመላቸውን ፕሮጀክቶችን ተሳቢ ያደረገ ነው ብሏል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት ከተመደበለት መደበኛ በጀት 74 ነጥብ 8 በመቶውን እንዲሁም የካፒታል በጀቱን 56 ነጥብ 8 በመቶ መጠቀም መቻሉን በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የዋይድ ኤርያ ኔትወርክ ተግባራዊ መደረጉ ባለጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት መመላለስ ሳይኖርባቸው ባሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን ለመከታተል የሚያስችል መሆኑን የገለፀው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለዚህ ፕሮጀክት ከተመደበው በጀት 98 በመቶ የሚሆነው ጥቅም ላይ መዋሉን አንስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ድካም የሚያቀሉ በመሆናቸው ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል።

#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews