EthiopiaNews

የአስመራ በረራ መቋረጥ መንስኤ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤርትራ የነበረኝ የገዛ ገንዘቤን እንዳላንቀሳቅስ በመታገዴ ምክንያት ወደ አስመራ አደርግ የነበረውን በረራ አቁሜአለሁ ብሏል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ጣቢያችን ኢቤኤስ ቴሌቪዥን በተገኘበት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስቀድሞ ይቀነስ ተብሎ የነበረው የአስመራ በረራ ቁጥር ተመልሶ እንዲጨምር ተጠይቆ ባለበት ሁኔታ ድንገት በረራ አቁሙ የሚል ደብዳቤ እንደመጣና ምክንያቱንም ለማወቅ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ኩባንያችን ኤርትራ ውስጥ ያለውን ገንዘብ እንዳያንቀሳቅስ በመታገዱ ወጪዎቹን ሸፍኖ ስራ ለመስራት አዳጋች ሁኔታ ስለተፈጠረበት በረራ ለማቆም ተገዷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ሳያቆም ለኤርትራ ባለስልጣናት 3 ጊዜ የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባቱን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይሁን እንጂ ጥረቱ ሳይሳካ መቅረቱን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡