የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድል ላስመዘገበው የአትሌቲክስ ቡድናችን ዳጎስ ያለ ሽልማት አበርክቷል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ18ተኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንጸባራቂ ድል ላስመዘገበው የአትሌቲክስ ቡድናችን ዳጎስ ያለ ሽልማት አበርክቷል፡፡ በዚህም ለልዑክ ቡድኑ በጋራ የ10ሚሊየን ብር ሽልማት ያበረከተ ሲሆን ሜዳልያ ላመጡ አትሌቶች ደግሞ ከአመታት መልስ የመሬት ስጦታ እንካቹ ብሏል። አራቱ የወርቅ ሚዳልያ ያመጡት አትሌቶች ማለትም አትሌት ለተሰንበት ግደይ፤ አትሌት ጎተይቶም ገ/ስላሰ፤አትሌት ታምራት ቶላ እና አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ እያንዳንዳቸው የ500 ካሬ ሜትር መሬት ሲሰጣቸው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በ1500ሜትር የብር ሜዳልያም በማምጣቷ ከመሬቱ በተጨማሪ በልዩ ተሸላሚነት በወርቅ ቅብ የተለበጠ የአዲስ አበባ መስተዳድር አርማ ያለበት ሳህን ስጦታ ተበርክቶላታል :: የብር ሜዳልያ ያስገኙት አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው ፤ አትሌት ለሜቻ ግርማ እና አትሌት ሞስነት ገረመው 350 ካሬሜትር መሬት ሲበረከትላቸው የነሃስ ሜዳልያ አሽናፊዎቹ አትሌት ዳዊት ስዩም እና አትሌት መቅደስ አበበ የ250 ካሬሜትር መሬት ባለቤት ሆነዋል፡፡መስተዳድሩ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉም በወርቅ የተለበጠ የመስተዳድሩ አርማ ያለበት የጌጥ ሰሃን በማበረከት አያት አደባባይን በስሟ የሰየመ ሲሆን በስሟ ትላልቅ ግንባታዎች እንደሚገነቡም አስታውቋል፡፡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምስጋናና ክብር መስጠት መርሃ ግብር ባደረጉት ንግግርም በድላችሁ ኢትዮጵያን ገፅታዋን ልታድሱ፥ ክብሯን በድል ልትገልጡ ፥ ሰንደቃችሁን አትማችሁ ኢትዮጵያን አስቀድማችሁ በ18 ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፊት ስላቆማችሁን ደስ ብሎናል እንኳን ደስ አለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።ሽልማቱ ምንም ነገር ሊሆን ይችላል ዋናው ነገር ክብር መስጠቱ ነው ያለችው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለሽልማቱ መስተዳድሩን አመስግናለች፡፡ አትሌቶቻችንም ከእኔነት ስሜት ይልቅ የኛነት ስሜትን ስላመጣቹ ላመሰኛችሁ እወዳለሁ በማለት ኢትዮጵያ ትደሰት፤ ትሩጥ ፤ ታሽንፍ፤ ትሳቅ ስትል ንግግሯን ቋጭታለች፡፡ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀJእላ መርዳሳ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ካቢኔው በዚህ ፍጥነት በተለይ የመሬት ስጦታውን በመወሰኑ በእጅጉ አመስግነዋል፡፡በኢትዮጵያ የህዝብ መዝሙር በተጀመረው እና ለ 30 ሰከንዶች ሞቅ ያለ ጭብጨባ በማድረግ ለአትሌቶቻችን ክብር በተሰጠበት በዚህ መርሃ ግብር በርካታ የመንግስት ሃላፊዎች እና የቀድሞ አትሌቶችም ተገኝተውበታል፡፡ ሪፖርተር ነቢል መሀመድ