የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 14ኛው የሕወሓት ጉባኤ መካሄድ አይችልም አለ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓት ነገ ሐምሌ 7 2016 ዓ.ም አደርገዋለሁ ያለው ጠቅላላ ጉባኤ ህጋዊ ሂደቶችን ያላለፈና መስፈርቶችን ያላሟላ በመሆኑ ሊደረግ አይችልም ብሏል።ቦርዱ ዛሬ ሐምሌ 6 2016 ዓ.ም ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ፓርቲው በተሻሻለው
የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ መሰረት በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ እውቅና እንደተሰጠው አስታውሷል።
ይሁንና ቦርዱ ውሳኔ የሰጠባቸውና ለጠቅላላ ጉባኤ መደረግ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለአብነትም ከጠቅላላ ጉባኤው 21 ቀናት አስቀድሞ ማሳወቅን : የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘትን የመሳሰሉ ጉዳዮች ባልተከናወኑበት ጉባኤው ሊካሄድ አይችልም ብሏል።
ጉባኤው ከቦርዱ እውቅና ውጭ የሚካሄድ ከሆነም ለጉባኤውም ሆነ በጉባኤው ለሚወሰኑ ውሳኔዎች እውቅና አልሰጥም ሲል አስታውቋል ።
ቀደም ሲል ሕወሃት በአመራሮቹ ዘንድ አወዛጋቢ የሆነውን ጉባኤ ከማካሄድ የሚያስቀረው ነገር እንደሌለ የገለጸ ሲሆን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ሕወሃት ለምርጫ ቦርድ መግለጫ የሰጠው ምላሽ የለም። የጉባኤው ተሳታፊዎችም መቀሌ ከተማ እየገቡ ይገኛሉ ።
ዜናውን ያጠናቀረው ኤርሚያስ በጋሻው ነው።