የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 24 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ተገለፀ።
ለዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ስኬትም ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለመስጠት አገልግሎቱ እያደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተከናውኗል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ560 ሺህ በላይ ተፈታኞች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ፈተናውን በበይነ-መረብ እንደሚወስዱም ተናግረዋል።
ለዚህም ተማሪዎች በቂ የኮምፒውተር ልምምድ የሚያደርጉበት አሰራር መዘርጋቱን አመላክተው፤ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ውስንነት ባሉባቸው አካባቢዎች ፈተናው በወረቀት እንደሚሰጥም ገልፀዋል።
ሀገር አቀፍ ፈተናውን ለሚወስዱ አካል ጉዳተኞችም ምቹ የመፈተኛ ከባቢን ለመፍጠርም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የፈተና ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢንተርኔት እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ያላቸውን ቀሪ ጊዜ በመጠቀም ለፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ ጠሰሪ ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሩ ተማሪዎች የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
