የ400 ሚሊዮን ዶላር ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል ተባለ

ከውጭ ተገዝቶ ወደውጭ የተሸጠው ነዳጅ::

አምና የ400 ሚሊዮን ዶላር ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል ተባለ

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ ከኢትዮጵያ ወደ 4 መቶ ሚሊየን ዶላር ገደማ የሚያወጣ ነው የተባለ የነዳጅ ዘይት በህገወጥ መንገድ ወደ ሌሎች አገራት መውጣቱ ተነገሯል።

ካፒታል ጋዜጣ ሪፖርቶችን ዋቢ በማድረግ በድረገጹ እንዳስነበበው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የደረስ ሲሆን አገሪቱ ነዳጅን ከውጭ ለማስገባት በየወሩ ከ250 ሚሊዮን ዶላር የበለጠ ወጪ ታወጣለች፡፡

ይህ ወጪም አገሪቱ የተለያዩ ምርቶቿን ወደውጭ ልካ ከምታገኘው ገቢ ጋር እንደሚስተካከል በመጠቆም ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ በሚወጣው የነዳጅ ዘይት ሳቢያ አገሪቱ ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሟታል መባሉን የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አህመድ ቱሳን ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡

በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ በህገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጣውን የነዳጅ ዘይት ለማስቆምም የነዳጅ ዘይቱ ዋና መተላለፊያ ናቸው ተብለዉ በተለዩት የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የነዳጅ ዘይት በኮታ ማከፋፈልን በአጭር ጊዜ መፍትሄነት መታሰቡ ተነግሯል፡፡

እንዲሁም በዘላቂ መፍትሄነት ደግሞ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም መንግስት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ በማንሳት የነዳጅ ዋጋን ከጎረቤት አገራት ጋር ለማቀራርብ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡